mesi

youngerversion

           ሙሉዋ ጨረቃ

 

ሙሉዋ ጨረቃ-ብሩኅ ነሽ ደማቃ

ታለቅሳለች ነፍሴ-ተስፋ ትቆርጥና

በውበትሽ ተማርካ-በመራቅሽ አዝና

ብሆን ከወለሉ አንቺም ጣሪያ ላይ

ዝቅዝቅ ከሚያዩትስ የሚያምር የለም ወይ?????

 

 

አንገትን ሲያቀኑ ብቻ ነው ማማሩ??

ያም ይሄም ያም ይሄም   አይንን ማጭርበሩ?

ፈክቶ መታየቱ ሽልምልም ማለቱ

በሩቅ ማጉዋጉዋቱ…………

 

 

ላይንም ሌላ አይን አለው

….

አንድን ጥሪኝ አፈር–ድንጋይ ብሎ ሚያስጥል በየጉራንጉሩ

ወርቅ ብሎ ሚያስቁዋጥር በየማህደሩ

እኔው ብሆን ነው ወይ የአይኔ አይን ባሪያ

ሳውቀው መሆንሽን የሌሎች አምሳያ

ጉልላት ያረኩሽ የፍጥረት እናት

በእውን የምትሞቂ ድንቅ የህልም እሳት

 

ዳኛ ነው የሚፈርድ ምክንያት ጠቃቅሶ መጽሃፍ አንብቦ

ግን ከሳሽ ተከሳሽ (ያው እንደኔና እንዳንቺው)

ስሜቱን አንግቦ

    እእምሮው ረግቦ

 

 

አውቃለሁ እንዳይሻር ይህ የብሉይ አዋጅ

ከአለኝታዬ አይጃጅ

በምኞቴ አይዋጅ

እንደነበር ሊኖር መታከት ….. መታከት …….መታከት

ነውንጂ……

 

ነውናም ስገብር ለአዋጁ ለእጣዬ

አንቺ ዝቅ ብለሽ ወይ እኔ ከፍ ብዬ

“እንገናኝ ይሆን?????” ሆኑዋል ጥያቄዬ

                             `1961 ዓ.ም

                             ደበበ ሰይፉ

                          ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ

                             

March 6, 2009 - Posted by meseret | mesi | | No Comments Yet

No comments yet.

Leave a comment