ትእግስትን ለማግኘት

ትእግስትን ለማግኘት
ሲጠሩ በጣም ቀላል ከሆኑ ለተግባር ግን ከሚከብዱ ቃላት አንዱ ትእግስት ነው፡፡አንድ ሰው ትእግስተኛ ተብሎ ለመጠራት በመከራ ቁዋት መዛቅና በችግር ቀንበር መደቆስ አልያም በእልህ አስጨራሽ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ግድ ይለዋል፡፡ያለበለዚያ እስከግዜው ድረስ “ያልተነካ” ከሚለው ስሙ ጋር ለመኖር ይገደዳል፡፡ለዚህ ይመስለኛል ብዙ ሰዎች ከእግዚአብሄር ትእግስትን ሲለምኑ የሚበረከተላቸው ነገር ተደራራቢ ችግርና እልህ አስጨራሽ ክስተት ብቻ የሚሆነው፡፡ነገሩ ግራ ይመስላል ግን ትክክል ነው፡፡አንድ ሰው ስለትእግስተኛነቱ ለማወቅ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል፡፡በአጠቃላይ ትእግስትን ለመማር ከተፈለገ ብቸኛው ትምህር ቤት ችግር ነው ማለት ይቻላል፡፡ምክንያቱም ትእግሰት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚታይ ጽናት ነው፡፡ችግር ከሌለ ጥናትም ሆነ ትእግስት ትርጉም የላቸውም፡፡
ብዙ ግዜ ሰዎችንም ሆነ ሁኔታዎችን ለመታገስ ጥረት አደርጋለሁ መጨረሻው ግን አያምርም፡፡ትእግስተኛ ለመሆን በጣርኩ ቁጥር ትእግስት-አልባ እየሆንኩ እመጣለሁ፡፡በመጨረሻ ሰአት ደግሞ ራሴን ትእግስተኛ አድርጌ ከመቁጠሬ የተነሳ ብሶት ሳሰማ እገኛለሁ፡፡
ሰዎችን መታገስ እንዲህ ተራራ ከሆነብኝ እግዚአብሄር ሁሉን የሚያውቀው (ክፋቴን ተንኮሌን አለመታዘዜን እርቃኔን የሚያየው) ደግሞ ምን ያህል ታግሶኝ ይሆን?ለመታገስ አስቸጋሪ የሆኑ ባህርያት ያለእፍረት ተሸክመን ቀኖቻችንን ስንገፋ ይህን ሁሉ በትዕግስት የሚያልፍ አባት እንዳለን እንኩዋን ልብ አንልም፡፡ከራሴ ብጀምር ግብዝ አስተሳሰቤ፣ቸልተኝነቴ፣አውቅ ባይነቴ፣ጭራውን መያዝ የሚያቅተው ተለዋዋጭ ስሜቴ ሌሎችም ባህሪያቴ የሰውን ጨጉዋራ ለመምለጥ በቂ እነደሆኑ አውቃለሁ፡፡ እንኩዋን ሌላ አካል ቀርቶ አንዳንዴ እኔው እራሴ ለራሴ እንጥፍጣፊ ምህረት አጣለሁ ፡፡ እንደዚህ አይነት ሆኜ ሳለ ይሄን ሁሉ ችሎ ታግሶኛል፡፡ሁላችንም ብንሆን ከተከናነብነው የታይታ ሽፋን ስር የአለማዊነት ኮተታችንና ጨምሮ ረዥም የአመጽ ባቢሎን ለመገንባት ከምናደርገው እፍረት የለሽ ጥረት የተነሳ ምህረት አይገባንም፡፡ ምስቅልቅል ህይወታችን ሀይል ለቅጽበት እንኩዋን በስጋ ለባሽ እጅ ቢገባ ያስጨርሰን ነበር፡፡
የሚገርመው ግን እግዚአብሄር ፍጥረትን ሁሉ ለዘመናት መታገሱ ነው፡፡ ታሪክን ማየት ይቻላል ከአዳም አለመታዘዝ እስከ ሄሮድስ የግፍ ጭፍጨፋ ከሰዶምና ገሞራ ግፍ እስከ አስቆረቱ ይሁዳ ክህደት ከእራኤል ማጉረምረም እስከ ስቅላቱ ድረስ የእግዚአብሄር ትእግስት ተዘርግቱዋል፡፡ አዳምና እኔ በመካከላችን ያሉትን ትውልዶች ጨምረን ባለመታዘዝ ስንዳክር እግዚአብሄር ትእግስት ታይቶብናል፡፡
ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ ይህንን ሃሳብ እናገኛለን፡፡
ከሓጥያተኞችም ዋና እኔ ነኝ ስለዚህ ግን የዘላለም ህይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን እየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በኔ ላይ ትእግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምህረትን አገኘሁ፡፡1 ጢሞ 1፡16
ፍቅርና ትእግስት
ከላይ በገልጥኩት ሁኔታ ሳልፍ ለምን መታገስ አቃተኝ?ፍቅር ስለሚጎለኝ ነው፡፡ ፍቅር ትእግስትን ቀላል እጅግ ቀላል ያደርገዋል፡፡ መታገስ የከባድ ድንጋይ ያህል ቢከብድም የሚወዱትን መታገስ ከገለባ የቀለለ ነው፡፡እውነተኛ ትግስት የፍቅር ውጤት እንጂ ብቻውን የቆመ ባህሪ ዐይደለም፡፡እግዚአብሄር ትእግስቱን እንድጋራው ይፈልጋል:: የሱ ሳያንስ እኔው ትግስተኛ እንድሆን መፈለጉ በጣም ያስገርማል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በመከራ እንድታገስ እንጂ ሰዎችን እንድታገስ አይመክረኝም ባይሆን እንድወዳቸውና ይቅር እንድላቸው እንጂ (ማቴ 18-22-25) ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ትእግስት እነዲሰጠኝ መጠየቁን እርግፍ አድርጌ ትቼዋለሁ ከፍቅር ጋር ሁሉንም እንደሚሰጠኝ ስለማውቅ፡፡

1 Comment »
Leave a comment
-
Archives
- November 2009 (2)
- June 2009 (1)
- May 2009 (2)
- March 2009 (2)
- February 2009 (6)
- January 2009 (3)
- July 2008 (2)
- June 2008 (5)
-
Categories
-
RSS
Entries RSS
Comments RSS

Thanks a lot for sharing this truth. At least now I know what to ask. Blessings!!