ምክሩዋ
“በዚህ ምድር ላይ ሶስት አላስፈላጊ ነገሮች አሉ” አለችኝ ፊቱዋን አኮማትራ “የመጀመሪያው ወንዶች ናቸው ሁለተኛውም ወንዶች ናቸው ሶስተኛው ብዙዎች እንደሚሉት ውሾች ናቸው::››
ተናደድኩ
“ምክንያታዊ ለመሆን ሞክሪ መቼም ቢሆን እደግመዋለሁ መቼም ቢሆን አፌን ሞልቼ ውሾች አላስፈላጊ ናቸው ልል አልችልም ፡፡ ” ተቀየምኩዋት፡፡ እቤቴ በገባሁ ቁጥር ነጭ ጭራዋን እያወዛወዘች ዘውድ ቀረሽ የንግስት አቀባበል የምታደርግልኝ ውሻዬ ቲቲ ከፊቴ ድቅን አለችብኝ፡፡
በርግጥ ለምድራችን ህልውና ካሰብን ማድረግ የሚገቡን ነገሮች የይኖራሉ ……ይህንኑ ልጠቁማት ሞክሬ ነበር እርሱዋ ግን የምትበገር አልነበረችም “ ትክክል ነሽ ችግሮች አሉ፡፡ማድረግ የሚገባን ነገር እንዳለም አልክድም፡፡
አንደኛ እናት ምድችንን ከእግር ኩዋስና ከቪድዮ ጌም ነጻ ማድረግ
ሁለተኛ ወንዶቻችን በአቅራቢያችን ወደምትገኘው ፕላኔት መሸኘት
ሶስተኛ በነሱ ምትክ ተሻሰሽለው የተሰሩትን ትናንሽ ቡችሎችና ነጫጭ ድመቶችን ወዳምድራችን ማስመጣት ይሆናል” አልኩዋት በጥበበኛነቴ የልብ ልብ እየተሰማኝ፡፡
ብዙም ሳይቆይ ሃሳቤን ውድቅ ለማድረግ ስትዘጋጅ ስላየሁዋት ፊቴ ዳመነ ፡፡ “ገና ልጅ ነሽ ማለት ነው” አለችኝ “ተሳስተሻል ወንዶች ብዙ ነገራቸው ከነቲቲ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ከስማቸው ልጀምር ሁለቱም የ”ወ”ቤተኛ ቃላት ናቸው፡፡ይሄንን ያወቅኩት” ‹ወ›ን መጥራት ባስጠላኝና የመንደራችንን ባለሱቅ ‹አወልን› ‹አሊ› ሰራተኛችንን ‹ወርቄን› ‹እርቄ› ብዬ መጥራት በጀመርኩበት ሰሞን ነው ፡፡
በጨለምተኛነቱዋ አዝኜ ለዘብ አልኩና…ቁዋንቁዋየን ቀይሬ በሴትኛ ላስረዳት ሞከርኩ. “እርግጥ ነው ወንዶች የውሾቻችንን ያህል ታማኝ አይደሉም ስትኮረኩሚያቸው ዝም ሊሉሽ አይችሉም ክብራቸውን ይወዳሉ፡፡ሲያዩሽ በደስታ ጭራቸውን አያወዛውዙም ሻሽ አስረሽ ቢያገኙሽ? አይልሡሽም አዎ… የውሾች ያህል አስደሳች አይደሉም ግን ቢሆንም ቢሆንም ይህን ያህል አሰልቺ ናቸው ብዬ አላስብም” ፡፡ለዚህ ነው ይህችው ጉዋዴ ባላዋቂነቴ ስሜቱዋ ተነክቶ ስለወንዶች ልትጽፍ ካሰበችው መጽሃፍ ውስጥ ጨልፋ ከሰፊው እውቀቱዋ ጥቂቱን ያጋራችኝ፡፡
ሀሁ ስለወንዶች
“አንድ ተራ ወንድ እንኩዋን ሲበዛ ጉረኛ ነው፡፡በሴቶች ፊት ተቀባይነት ለማግኘት የማያደርገው ጥረት የለም ለክብሩ ከመሞት ወደሁዋላ አይልም፡፡ አንዲት ሴት ወደድኩህ እንድትለው የሞት ጉድጉዋድ ቢሆን ከመማስ አይመለስም ፡፡ ስለዚህ ነገር ባታስብ እንኩዋን በቀናት በወራትና በአመታት ጉትጎታ እንድታስብ ያደርጋታል ከዚያ ተጋብተው በደስታና በፍቅር በሰላምም ይኖራሉ፡፡…እንግዲህ ምን እንላለን…….አይደለም… ይቅርታ ወደሁዋላ ልመልስሽና ባታስብ እንኩዋን በቀናት በወራትና በአመታት ጉትጎታ እንድታስብ ያደርጋታል፡፡ማሰብዋን ካወቀ በሁዋላ ግን ይረጋጋል መረጋጋት ብቻ ሳይሆን ይንሰራፋል፡፡ የነገን በር በጁ ጠቁሞ ካሳያት በሁዋላ ባልታወቀ ሁኔታ ደርሶ አይነስውር ይሆናል (ለጉርሻ እጁን ዘርግቶ መልሶ እንደሚነሳ ሰው ማለት ነው ይታይሽ የተከፈተ አፍኮ መልሶ ለመዝጋ እንኩዋን እፍረት ነው) ፡፡መድረሻቸውን ከሩቅ አሳይቶ ካስረዳት በሁዋላ ይዘነጋውና መልሶ የት እንደሚሄዱ ይጠይቃታል (ቂቂቂ) ፡፡ ነገሩያልገባት ሆዬ ዘንግቶት መስሉዋት ልትመራው ከዘራውን ትቀበለዋለች አለቀላት በቃ ከዚያ በሁዋላ እሱዋ መሪ እሱ ተመሪ ይሆናሉ፡፡ወደሁዋላ መቅረቱ ሳያንስ አንዳንዴ ተገትሮ አልንቀሳቀስ ሊልም ይችላል፡፡የጉድ ቀን አይመሽም እንዲሉ አንገቴን አንቃ ልታገባኝ ነው እያለ ይለፍፋል፡፡ መለፈፊያ ካላገኘም ለቅርብ ጉዋደኞቹ ይህንኑ ያሳስባል፡፡በመጨረሻ እሱዋ የምትሆነው የታሪኩ ማዳመቂያ ብቻ ይሆናል”አቀማመጡዋን አስተካከለች “ገባሽ?” አለችኝ “ግራ ገባኝ” አልኩዋት፡፡
”ቀለል ባለ መልኩ ላስረዳሽ”
ሶስት ደረጃዎች?
“ከወንዶች ጋር የምታሳልፊውን ግዜ በሶስት ከፍለን ልናየው እንችላለን በዚህ ሂደት ውስጥ የመጀመሪያ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃዎችን ልታልፉ ትችላላችሁ፡፡የመጀመሪያውና ሁለተኛው ደረጃ አስደሳች እና በእርጋታ የተሞላ ቢሆንም ሶተኛውን ግን እመኚኝ የትኛዋም ሴት ልትቁዋቁዋመው አትችልም፡፡
የመጀመሪያ ሰሞን
ያብዳል ይነጠፋል ይርበተበታል ያለቅሳል የማይሆነውን መናገሩ ይቀላል አወራሩ አረማመዱ አስተያቱ ሁሉም ነገር በፍቅር የተቃኘ (romantic) ነው፡፡እኔ የሚለውን ቃል ከመዝገበ ቃላቱ ሰርዞ አንቺ በሚለው ይተካዋል ፡፡
‹‹የኔ ውድ ሳላገሽ ሁለት ቀን ሆነኝ ምን ይሻለኛል››
“ስማኝ”
“ምን ማለትሽ ነው የኔ ፍቅር አንቺ ተናግረሽ?ለምን ዘላለም አትናገሪም እየሰማሁሽ እሞታለሁ”
“ግዜ ስጠኝ”
“ከምኔ ላይ ልስጥሽ ግዜዬ ሁሉ ያንቺ ነው “እዩዋት ስትናፍቀኝ …………”
“ክፈል”
“ለመክፈል እንዳታስቢ ቤት ተከራዪ እኔ እከፍላለሁ ተደሰቺ ብዪ ጠጪ ስለሂሳቡ እንዳታስቢ የስሜን የመጀመሪያ ፊደል መጥራት ብቻ ነው የሚጠበቅብሽ በብርሃን ፍጥነት ካጠገብሽ እገኛለሁ፡፡ your wish is my command ይላሉ ያገሬ ሰዎች ወደሽ ከተደፋሽ ለማለት ነው፡፡ ”
“አደናቀፈኝ”
“እኔ ልነጠፍልሽ፡፡ የዘንድሮ ድንጋይ ደግሞ አበዛው እየመረጠ አይመታም እንዴ?”
ከወራት በሁዋላ
ይረጋጋል ክብሩን በመጠበቅ ላይ ያተኩራል፡፡ስሜትሽን ላለመጉዳት ሲል ይዋሻል መዋሸቱ ከታወቀ እንደመቆጣትም ያደርገዋል፡፡በዚህ ደረጃ ክርክር ይበዛል አንቺ በእኔ ይተካል ፡፡
“የኔ ውድ ሳላገኝሽ አንድ ወር ሆነኝ ምን ላርግ ስራዬ ሁኔታ እንደምታውቂው ነው፡፡ያም ሆኖ ሁሌ አስብሻለሁ”
“ክፈል”
“ዝርዝር ይኖርሻል?”
“ግዜ ሥጠኝ”
“እንዴት እንዲህ አይነት ጥያቄ ትጠይቂያለሽ ከኔ በላይ አንቺ አትጨነቂም ግን ምንም ላደርግ አልቻልኩም ስንት ነገር አለ መሰለሽ ስራ ንግድ የጉዋደኛዬ ሰርግ በዛ ላይ አደራ የተባልኩት ነገር…….ኡ ልሞት ነው፡፤”
“አደናቀፈኝ”
“ምን ሆነሻል የኔ ውድ እያየሽ ሂጂ እንጂ ወይ አይንሽን ተመርመሪ”
አመታት ሲያልፉ
ክርክር ጋብ ይላል በየአጋጣሚዎች ብቻ ሞቅ ያለ ጠብ ይኖራል አንዱ ሳይፈታ ሌላ ይደረባል ፡፡
“አዎ አልደወልኩልሽም ልደውልልሽ አልቻልኩም የኔ ጥፋት ኤደለም አትጨቅጭቂኝ
ሴትዮ እኔን ከመጨቅጨቅ ሌላ ስራ የለሽም እንዴ?ስፈልግሽ እኔ ራሴ እደውልልሻለሁ”
“ስማኝ”
“ቆይ አዳምጪ ቤተሰቦችሽ በድለውሻል ለምን ሁልግዜ ያንቺ ብቻ እንዲሰማ ትፈልጊያለሽ፡፡ የሰውን ሃሳብ የመስማት ባህል አዳብሪ”
“ክፈል”
“በህይወቴ እንዳንቺ አይነት ስግብግብ ሴት አይቼ አላውቅም መክፈል የሚባል ነገር አለ ”
“አደናቀፈኝ”
“እንግዲህ ጣጣሽን አታብዢ እያየሽ ሂጂ ብዬ ብዙ ግዜ ነግሬሻለሁ መፈክር ከሆነም ሌላ ቀይሪ “
ይሀው ነው እንግዲህ” አለችኝ በመጨረሻ ከተቀመጠችበት እየተነሳች ፡፡
“መቼም ወንድ ሁሉ እንዲህ ሊሆን አይችልም ያንቺ ጠባብ እይታ ከሚሸፍናቸው ቦታዎች ውጪ በተቃራኒው የሚያስቡ፤ የሚጠነቀቁ፤ ምክንያታዊነት ያልራቃቸው፤ ጥሩ ወንዶች ይኖራሉ ለምሳሌ እኔ ከማውቃቸው ውስጥ እንዲህ አይነቶቹን ልጠቅስልሽ እችላለሁ …………”ሃሳቤ ተምታታብኝ፡፡”ሚካዔል? ገብርኤል …?ሳጥናኤል?” ????????????????? ”? ራሴን ጠይቄ ሳልጨርስ ልትሄድ ተነሳች፡፡ ሳትሄድ ማስረጃዬን ለማቅረብ አይምሮዬን አስጨነቅኩት … ፡፡
”እሺ በቃ ቢያንስ የውሾቹን አርሚ” አልኩዋት ከበሩ አጠገብ እንደደረሰች ተስፋ ቆርጬ ፡፡”መቼም ቢሆን ውሾች አላስፈላጊ አይደሉም ቢያንስ ወንዶች ላይ ይጮሃሉ”
ትእግስትን ለማግኘት

ትእግስትን ለማግኘት
ሲጠሩ በጣም ቀላል ከሆኑ ለተግባር ግን ከሚከብዱ ቃላት አንዱ ትእግስት ነው፡፡አንድ ሰው ትእግስተኛ ተብሎ ለመጠራት በመከራ ቁዋት መዛቅና በችግር ቀንበር መደቆስ አልያም በእልህ አስጨራሽ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ግድ ይለዋል፡፡ያለበለዚያ እስከግዜው ድረስ “ያልተነካ” ከሚለው ስሙ ጋር ለመኖር ይገደዳል፡፡ለዚህ ይመስለኛል ብዙ ሰዎች ከእግዚአብሄር ትእግስትን ሲለምኑ የሚበረከተላቸው ነገር ተደራራቢ ችግርና እልህ አስጨራሽ ክስተት ብቻ የሚሆነው፡፡ነገሩ ግራ ይመስላል ግን ትክክል ነው፡፡አንድ ሰው ስለትእግስተኛነቱ ለማወቅ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል፡፡በአጠቃላይ ትእግስትን ለመማር ከተፈለገ ብቸኛው ትምህር ቤት ችግር ነው ማለት ይቻላል፡፡ምክንያቱም ትእግሰት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚታይ ጽናት ነው፡፡ችግር ከሌለ ጥናትም ሆነ ትእግስት ትርጉም የላቸውም፡፡
ብዙ ግዜ ሰዎችንም ሆነ ሁኔታዎችን ለመታገስ ጥረት አደርጋለሁ መጨረሻው ግን አያምርም፡፡ትእግስተኛ ለመሆን በጣርኩ ቁጥር ትእግስት-አልባ እየሆንኩ እመጣለሁ፡፡በመጨረሻ ሰአት ደግሞ ራሴን ትእግስተኛ አድርጌ ከመቁጠሬ የተነሳ ብሶት ሳሰማ እገኛለሁ፡፡
ሰዎችን መታገስ እንዲህ ተራራ ከሆነብኝ እግዚአብሄር ሁሉን የሚያውቀው (ክፋቴን ተንኮሌን አለመታዘዜን እርቃኔን የሚያየው) ደግሞ ምን ያህል ታግሶኝ ይሆን?ለመታገስ አስቸጋሪ የሆኑ ባህርያት ያለእፍረት ተሸክመን ቀኖቻችንን ስንገፋ ይህን ሁሉ በትዕግስት የሚያልፍ አባት እንዳለን እንኩዋን ልብ አንልም፡፡ከራሴ ብጀምር ግብዝ አስተሳሰቤ፣ቸልተኝነቴ፣አውቅ ባይነቴ፣ጭራውን መያዝ የሚያቅተው ተለዋዋጭ ስሜቴ ሌሎችም ባህሪያቴ የሰውን ጨጉዋራ ለመምለጥ በቂ እነደሆኑ አውቃለሁ፡፡ እንኩዋን ሌላ አካል ቀርቶ አንዳንዴ እኔው እራሴ ለራሴ እንጥፍጣፊ ምህረት አጣለሁ ፡፡ እንደዚህ አይነት ሆኜ ሳለ ይሄን ሁሉ ችሎ ታግሶኛል፡፡ሁላችንም ብንሆን ከተከናነብነው የታይታ ሽፋን ስር የአለማዊነት ኮተታችንና ጨምሮ ረዥም የአመጽ ባቢሎን ለመገንባት ከምናደርገው እፍረት የለሽ ጥረት የተነሳ ምህረት አይገባንም፡፡ ምስቅልቅል ህይወታችን ሀይል ለቅጽበት እንኩዋን በስጋ ለባሽ እጅ ቢገባ ያስጨርሰን ነበር፡፡
የሚገርመው ግን እግዚአብሄር ፍጥረትን ሁሉ ለዘመናት መታገሱ ነው፡፡ ታሪክን ማየት ይቻላል ከአዳም አለመታዘዝ እስከ ሄሮድስ የግፍ ጭፍጨፋ ከሰዶምና ገሞራ ግፍ እስከ አስቆረቱ ይሁዳ ክህደት ከእራኤል ማጉረምረም እስከ ስቅላቱ ድረስ የእግዚአብሄር ትእግስት ተዘርግቱዋል፡፡ አዳምና እኔ በመካከላችን ያሉትን ትውልዶች ጨምረን ባለመታዘዝ ስንዳክር እግዚአብሄር ትእግስት ታይቶብናል፡፡
ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ ይህንን ሃሳብ እናገኛለን፡፡
ከሓጥያተኞችም ዋና እኔ ነኝ ስለዚህ ግን የዘላለም ህይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን እየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በኔ ላይ ትእግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምህረትን አገኘሁ፡፡1 ጢሞ 1፡16
ፍቅርና ትእግስት
ከላይ በገልጥኩት ሁኔታ ሳልፍ ለምን መታገስ አቃተኝ?ፍቅር ስለሚጎለኝ ነው፡፡ ፍቅር ትእግስትን ቀላል እጅግ ቀላል ያደርገዋል፡፡ መታገስ የከባድ ድንጋይ ያህል ቢከብድም የሚወዱትን መታገስ ከገለባ የቀለለ ነው፡፡እውነተኛ ትግስት የፍቅር ውጤት እንጂ ብቻውን የቆመ ባህሪ ዐይደለም፡፡እግዚአብሄር ትእግስቱን እንድጋራው ይፈልጋል:: የሱ ሳያንስ እኔው ትግስተኛ እንድሆን መፈለጉ በጣም ያስገርማል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በመከራ እንድታገስ እንጂ ሰዎችን እንድታገስ አይመክረኝም ባይሆን እንድወዳቸውና ይቅር እንድላቸው እንጂ (ማቴ 18-22-25) ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ትእግስት እነዲሰጠኝ መጠየቁን እርግፍ አድርጌ ትቼዋለሁ ከፍቅር ጋር ሁሉንም እንደሚሰጠኝ ስለማውቅ፡፡

-
Archives
- November 2009 (2)
- June 2009 (1)
- May 2009 (2)
- March 2009 (2)
- February 2009 (6)
- January 2009 (3)
- July 2008 (2)
- June 2008 (5)
-
Categories
-
RSS
Entries RSS
Comments RSS


